የሰላምና አንድነት ጉባኤ ዓላማ

"ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን"

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ የተቋቋመበት ዋና ምክንያት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በመስቀሉ ጥልን ገድሎ ሰውና እግዚአብሔርን ሕዝብንና አሕዛብን ያገናኘውን የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በመስበክ፣ሰውንና እግዚአብሔርን ስታስታርቅ የኖረች ጥንታዊት፤ ሐዋርያዊትና ታሪካዊት መሆኗ፣ በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በእኛ ጊዜ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ምክንያት በአባቶች መካከል የተፈጠረው ልዩነት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን በከፍተኛ ችግር ላይ እንድትገኝ አድርጓታል። ልጆቿም የቤተ ክርስያናቸውን የውስጥና የውጭ ጠላቶች አንድ ልብና አንድ ቃል ሆነው እንዳይመክቱ፣ ጊዜያቸውንና ኃይላቸውን በእርስ በርስ ውዝግብ እንዲያጠፉት አድርጓቸዋል። በዓለም የዜና ማሰራጫዎችና ድረ-ገጾች፣ በቤተ ክርስቲያን ስም የእርስ በርስ ውዝግብን መስማት የተለመደ ሆኗል። ይህም፣ የቤተ ክርስያኒቱን መንፈሳዊ ሕይወት እጅጉን ጎድቶታል። የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናንም በተፈጠረው ችግር ግራ ተጋብተው በኃዘንና በጸሎት ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ለነገ የማይባል መሠረታዊ የሕልውና ጉዳይ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን በንድነት  ጸንታ እንድትኖር የአባቶች አንድነት አስፈላጊ በመሆኑ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ሰላምና አንድነት ለመስራት የተቋቋመ  የሰላም ጉባኤ ነው።
የሰላም ጉባኤው አባላትም  በቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው በአባቶች መካከል ሰላም ሰፍኖ ማየት የሚፈልጉ፤ አባቶች በሕይወት እያሉ ችግሩ መፈታት አለበት እንጂ ወደ ትውልድ መተላለፍ የለበትም ብለው የሚያምኑ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሕብረት ነው።

 የሰላም ጉባኤው እንዴት ተጀመረ?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ መነሻ ምክንያቶች፣
ሀ) የብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ሊቀ ጳጳስ ዕረፍት፤
ለ) የብፁዕነታቸውን እረፍት አስመልክቶ ስለ መካነ መቃብራቸው ከያቅጣጫው  የቀረበው አስተያየትና፣
ሐ) ከአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ «ወደ አገራቸው መጥተው ይቀበሩ» ሲል የሰጠው መግለጫ ናቸው። ብፁዕነታቸው ንዳረፉ፣ በሁሉም ዘንድ ከፍተኛ ኃዘን ተፈጥሮ ነበር። ይልቁንም የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ሳያዩ በማረፋቸው፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለሆኑ ሁሉ ትልቅ ኃዘን ነበር። ይሁን እንጅ ለብዙዎቹም፣ የብፁዕነታቸው ዕረፍት፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ምክንያት ይሆናል የሚል ጽኑ ተስፋ አሳደረባቸው። በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጠው መግለጫም፣ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ትልቅ በር ከፋች ይሆናል ብለው ያመኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች፣ የሰላሙን ጥረት ሊጀምሩ ችለዋል።

ብዙዎቹ የሰላም ጉባኤው አባላት በብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ዕረፍት ምክንያት የተገናኙ ናቸው። መሠረታዊ መነሻውም አባቶች በሕይወት እያሉ በእነርሱ ዘመን የተፈጠረው ችግር በእነርሱ ካልተፈታ፣ ለቀጣዩ ትውልድ አንዲት ቤተ ክርስቲያንን ለማስረከብ ከባድ መሆኑን በመገንዘብ፣ አባቶችም የሚወዷት ቤተ ክርስቲያን አንድ ሆና ሳያዩአት እንዳያልፉ፣ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን አንድነት ልባቸው አርፎ፣ ሳይለያዩ በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ ለማድረግ ነው።

ዓላማ፣ ግብና አቋም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባዔ ዓላማው ቤተ ክርስቲያንን አንድ ማድረግ ነው። ግቡ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ማየት ነው፤ አቋሙ በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙትን አባቶች በአክብሮትና በእኩልነት በማየት ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት መሥራት ነው። ይህንንም የሚገልጽ የሥራ መመሪያ አውጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል።

አገልግሎት
ጉባኤው እስከ ዛሬ ሁለት ጉአባኤያተ አበውን አስተናገዷል።  ለዚህም  አንባቢ  መገለጫዎቹን እንዲመለከቱ እንጋብዛለን።


  " ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን =ስለቤተ ክርስቲያና ሰለም ጸልዩ"