Friday, October 19, 2012

10/15/2012
ጥቅምት 5/2005ዓ/ም

ወቅታዊውን የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ አስመልክቶ የወጣ መግለጫ።

 
“ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።”
 

          ጥንታዊትና ሐዋርያዊት፣ ብሔራዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም እንደ ቀድሞው አንድነቷ ጸንቶ ልትቆም፣ ሕዝቦቿንም ልትሰበስብና በሰላምና በአንድነት ጸንተው እንዲኖሩ ተግታ ማስተማር እንድትችል መጀመሪያ በመሪዎቿ መካከል ያለውን ልዩነት በአንድነት ልትለውጠው ይገባል። ይህም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ እምነት ነው። እነሆ በዘመናችን ከሁለት ከሦስት ተከፍላ ልጆችዋም እንደ ጠላት ማዶ ለማዶ የሚተያዩበት ዘመን ሊያከትም ይገባዋል። ምክንያቱም ይህ ልዩነት የቤተ ክርስቲያኒቱን የረጅም ዘመን ታሪክና መንፈሳዊ አቋም በእጅጉ ከማዛባቱም በላይ በልጆቿም መካከል ፍቅርን እያጠፋና ኃይሏን እያዳከመ ስለሚገኝ ነው። ክፍፍሉም የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንና የሀገራችን የኢትዮጵያን አንድነት ልውና ለማይፈልጉም ትልቅ በር ከፍቶላቸዋል። በአባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት፣ ከሁለቱም አቅጣጫ የተላለፈው ውግዘት፣ በዜና አውታሮች የሚሰማውና በድረ ገጾች የሚነበበው መነቃቀፍ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች መንፈሳዊ ስሜት እጅጉን ጎድቶአል። ታላቋን ቤተ ክርስቲያን የሚያከብሩትን ኢትዮጵያውያንም አሳፍሯል፤ ይህ ያሳሰባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናንም በታላቅ ኀዘንና ጸሎት ላይ ይገኛሉ።

 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ዋና ተግባር በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች አባቶቻችን ልዩነታቸውን ለማስወገድና የቤተ ክርስቲያንን ችግር በውይይት ለመፍታት እንዲችሉ የሰላምና የአንድነት መድረክ ማመቻቸትና ችግሩ ለዘለቄታው እንዲፈታ ተግቶ መሥራት ነው።

 
የሰላምና አንድነት ጉባኤው ዓላማ፣ አቋምና ግብ እንዲሁም ያካሔዳቸው ጉባኤያት

          የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ዓላማው ቤተ ክርስቲያንን አንድ ማድረግ፣ ግቡ የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት ማየት፣ አቋሙ በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙትን አባቶች በአክብሮትና በእኩልነት በማየት ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ጠንክሮ መሥራት ነው። ይህንንም በአጽንዖት የሚገልጽ የሥራ መመሪያ አውጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል። ጉባኤው ከዚህ በፊት የመጀመሪያውን ጉባኤ አበው  ከሐምሌ 26-28, 2002 (August 2-5/2010) Hilton McLean Tysons Corner 7920 Jones Branch DR Virginia 22102 ማዘጋጀቱና በኢትዮጵያና በውጭ ሀገር በሚገኙ አባቶች መካከል የሰላም ንግግር እንዲጀመር ማድረጉ ይታወሳል። ሁለተኛውን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ደግሞ በአሪዞና ክፍለ ግዛት  ከየካቲት 2-9, 2004 /ም(February 10-17/2012) ማካሄዱ ይታወቃል። በመቀጠልም ሦስተኛውን ጉባኤ አበው በማዘጋጀት ላይ እንዳለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በድንገት በማረፋቸው ጉባኤው የተሰማውን ኃዘን ገልጿል። ከዚህም ጋር በነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም. ልዑካንን ሰይሞ ወደ አትዮጵያ በመላክ በቅዱስነታቸው አባታዊ ቡራኬና በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ንግግር ከመቼውም በበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት ፍጻሜ ስለሚያገኝበት ሁኔታ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጽሑፍና በቃል ማብራሪያ አማካይነት አቅርቦ ውይይት እንዲካሔድ በማድረግ የዕርቀ ሰላሙን ቀጣይነት ከቅዱስ ሲኖዶስ በተጻፈለት ደብዳቤ አረጋግጧል።

  
          ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወሰላመ እግዚአብሔር እንተ ኩሉ ባቲ፣ ወትትሌዓል እምኩሉ ልብ፣ ታጽንኦ  ለልብክሙ ወለህሊናክሙ በኢየሱስ ክርስቶስ” (ፊልጵ. 4፥8) ሲል የሰበካትን ሁሉ ያለባትን፣ ለሁሉ የምትጠቅም ክብረ ሥጋ፣ ክብረ ነፍስ የሚገኝባትን፤ ሕይወተ ሥጋ ወነፍስ፤ ዕርገተ ጸሎት ወመሥዋዕት የሚከናወንባትን የቤተክርስቲያንን ሰላምና አንድነት መንገድ ለመፈለግና ዕርቀ ሰላም ለመመሥረት በጥቅምት ወር በሀገር ውስጥና  በውጭ ሀገር ከሚካሔደው ጉባኤ ሲኖዶስ ወሳኝ አቋምና ሰላምን የሚያስቀድም ውሳኔ ይጠበቃል። በመሆኑም በውጭም ሆነ በውስጥ የሚኖሩ አባቶቻችን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በመላው ዓለም የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ በጉጉት የሚጠብቁትን የቤተ ክርስቲያን የአንድነት ቀን ያበሥረናል፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ለቤተ ክርስቲያናቸው ያላቸውን ፍጹም አክብሮትና ፍቅር የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በማስቀደም ያከበረቻቸውን ቤተ ክርስቲያን ለወደፊት ተለያይታ ከመቅረት ይታደጓታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

በቅርቡ ከሚካሔደው የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ መልዓተ ጉባኤ ምን ይጠበቃል?

1ኛ/ እናት ቤተ ክርስቲያንን ወደ ቀደመ ክብሯ ለመመለስ ታሪካዊ ሥራ መሥራት፤ ከራስ ክብር ይልቅ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ማስቀደም፤
 

2ኛ/ ባለፈው ችግር ላይ ጊዜን ከማጥፋት ይልቅ በመፍትሔው ላይ በማተኮር ወደፊት ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልገውን የሰላምና አንድነት መሠረት መጣል፤

3ኛ/ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት 21 ዓመታት በልዩነትና በክፍፍል ጉዞዋ በዓለም ፊት ያስመዘገበችውን አሳዛኝና አሳፋሪ የልዩነትና የክርክር ምዕራፍ ዘግቶ የሰላምና አንድነትን ዜና ማብሰር፤
 

4ኛ/ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በእርስ በእርስ ልዩነት የሚያጠፉትን ጊዜ፣ የጠፋውን በመፈለግ፣ የተበተነውን መንጋ በመሰብሰብ ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የኅብረተሰቡን የአስተሳሰብ ደረጃ የጠበቀ፣ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያንን ሁልጊዜ በመምህርነትዋ እንድትቀጥል የሚያደርግ የሊቅነት ሥራ እንዲሠሩ ለማድረግ አንድነቷና ሰላሟ የሚመለስበትን ታሪካዊ ሥራ መሥራት።

5ኛ/ ሕዝባችን ከዕለት ወደ ዕለት በአባቶቹ እያፈረና በዚህም ተነሣ ከእናት ቤተ ክርስቲያን እየራቀ እንዳይሔድ በዘመናችን የተከፈቱትን የመከፋፈልና የመወጋገዝ በሮች በመዝጋት የክርስቶስ መንጋ በሰላምና በፍቅር ወጥቶ የሚገባበት ዘለቄታዊ የሰላምና አንድነት በር እንዲከፈት የሚያደርግ ሐዋርያዊ ተግባር ከጥቅምቱ ሲኖዶስ ይጠበቃል።
 

          ከምንም በላይ ደግሞ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳውያን አባቶች እንደተወጋገዙ በሞተ ሥጋ ማለፍ ለቤተ ክርስቲያን ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ ከአባቶች የተሠወረ አይደለም። እንደሚታወቀው በርካታ አባቶቻችን  የቤተክርስቲያናቸውን የሰላምና አንድነት ቀን ሳያዩት በሞተ ሥጋ እያለፉ ነው። ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚገኙት ሊቃነ ጳጳሳት ይህን የታሪክ አጋጣሚ ተጠቅመው የቤተ ክርስቲያን ችግር  ለዘለቄታው በመፍታት የቤተክርስቲያንን የልዩነት ታሪክ እንደሚለውጡት ተስፋችን ጽኑ ነው። ስለዚህ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የምትገኙ ክቡራን አባቶቻችን ሊቃነ ጳጳሳት እግዚአብሔር የከፈተውን የሰላም በር ተጠቅማችሁ የምትሠሩት ሥራ ከታሪክ ተወቃሽነት የሚያድን ብቻ ሳይሆን በእውነት ዕርግናችሁ የክብርና የድል እንዲሆን የሚያደርግ፣ እያዘኑ ከማለፍ የሚያድን የአገልግሎታችሁ ዘውድ ላከበረቻችሁም ቤተ ክርስቲያን ለዘወትር ክብርና ሞገስ ይሆናል ብለን በእጅጉ እናምናለን።
 

በውጭ ሀገር የሚኖሩትን አባቶች በተመለከተ  

          በውጭ አገር የሚገኙት አባቶች ለተጀመረው የቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ጉዞ እንቅፋት የሚሆን ማንኛውም ዓይነት መግለጫ በቃልም ሆነ በጽሑፍ ከመስጠት እንዲቆጠቡ በታላቅ ትሕትና እንጠይቃለን።  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስንና በስደት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን ባነጋገረበት ወቅት ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ወደ ኤርትራ ያደረጉትን ጉዞ ቅዱስ ሲኖዶስ በፍጹም እንደማያውቀውና ቅዱስ ሲኖዶስንም እንደማይወክል በመግለጽ፣ ይልቁንም ብፁዕነታቸው ጉዞውንም ያደረጉት በግላቸው መሆኑን ለሰላምና አንድነት ጉባኤው በአጽንዖት አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙትን አባቶች በተመለከተ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  የሰላምና  አንድነት ጉባኤ በቅድስት አገር ኢትዮጵያ ለሚገኙት መላው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከታላቅ አደራ ጋር ማሳሰብ የሚፈልገው ዐቢይ ጉዳይ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በምትገኙት ብፁዓን አባቶች መልካም ፈቃድ የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት ከፍጻሜ ሳይደርስ በመካከል ሌላ  ፓትርያርክ ቢመረጥ ቤተ ክርስቲያናችን ለፉት ሃያ ዓመታት ተከፋፍላ ካሳለፈችው አሳፋሪና አሳዛኝ ታሪክ እጅግ ወደ ባሰና ውስብስብ ወደሆነ ችግር ውስጥ እንድትወድቅ ያደርጋታል ስለሆነም ከዚህ ፈተና ለመዳን ብቸኛው መፍትሔ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የምትገኙት ብፁዓን አባቶች በጋራ ተወያይታችሁ፣ ያለፈውን ችግር በውይይት ፈትታችሁ፤ የልዩነት ታሪካችንን በአንድነት አድሳችሁ ለወደፊቱ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይበጃል የምትሉትን ማናቸውንም መፍትሔ በጋራ ኃላፊነት ወስዳችሁ በአንድነት ተግባራዊ እንድታደርጉ በታላቅ ትሕትናና አክብሮት እንጠይቃለን። ይህ ካልሆነ ግን በአገር ውስጥም ሆነ አገር ውጪ ያሉት አባቶች ሌላ ፓትርያርክ እየሾሙ ለዘለቄታው በልዩነት እንዲኖሩ በር ከመክፈቱም በላይ ቀሪውን የአገልግሎት ዕድሜያችሁንንም በልዩነት የሚያሳልፍ በመሆኑ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስትሉ ከሁሉ አስቀድማችሁ ላለፉት ሃያ ዓመታት የቆየውን የልዩነት ምዕራፍ በፍጹም ኅብረትና አንድነት እንድትዘጉት የሰላምና አንድነት ጉባኤው በአክብሮት ይማጸናችኋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትን በተመለከተ

 እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ለሕዝባችን ሰላምና አንድነት መሠረት መሆኑ ይታመናል። ስለዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥትም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት አስመልክቶ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግና ብፁዓን አባቶችም ያለ አንዳች ጣልቃ ገብነት/ተጽእኖ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት የሚበጀውንና ተገቢውን ውሳኔ በራሳቸው እንዲያስተላልፉ መሉ ትብብር እንዲያደርግ የሰላም ጉባኤው በአጽንኦት ይጠይቃል። የቤተ ክርስቲያኒቱ መከፋፈል ለትውልድም ሆነ ለአገርም የማይበጅ በመሆኑ ለተጀመረው የዕርቀ ሰላም ሒደት ስኬታማነት ቤተ ክርስቲያንን በሚያስፈልገው ተገቢ መንገድ በማገዝና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጽእኖ ባለማድረግ ይተባበር ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።

          በመጨረሻም የቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ካህናት ወምእመናን አካላችንን ቤተ ክርስቲያንን የለያያት ችግር ለዘለቄታው ተወግዶ ፍጹም ሰላምና አንድነት እንዲሰፍንባት ዘወትር ነቅተንና ተግተን ልንጸልይ ይገባል። በመሆኑም ስለ አንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንድታሰሙ በትሕትና እንጠይቃለን።

 “ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ!”
 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  የሰላምና  አንድነት ጉባኤ።