Wednesday, December 12, 2012

የ3ኛው ጉባኤ አበው የኢ ኦ ተ ቤ ክ የሰላምና አንድነት ጉባባኤ መግለጫ



 

 
  ኅዳር30/2005 /
12/9/2012

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ሦስተኛውን  ጉባኤ አበው አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ።

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ  ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ አዘጋጅነት በዳላስ ቴክሳስ ክፍለ ግዛት ከኅዳር 25-30/2005 ዓ/ም በሚካሄደው ጉባኤ ለመገኘት ከሀገራችን ኢትዮጵያ የመጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ  ልዑካንና   በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ በስደት ላይ ከሚገኘው  የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ  ቅ/ሲኖዶስ  ልዑካን በተገኙበት 3ኛውን ዙር ንግግር አካሂዷል።  የጉባኤው ዋና ዓላማም ላለፉት 21 ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን ይከፋፈላትን ችግር ለመፍታትና አንደነቷን ለመመለስ ሲሆን በጉባኤው ላይ የተገኙ ልዑካንም፦

ከኢትዮጵያ

1.     ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ

2.    ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ሊቀ ጳጳስ

3.    ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሊቀ ጳጳስ

4.    ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሓ

      ከሰሜን አሜሪካና አውሮፓ

1.     ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ሊቀጳጳስ

2.    ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ሊቀጳጳስ

3.    ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሊቀጳጳስ

4.    ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ናቸው 

የሰላምና አንድነት ጉባኤው  የሁለቱን  ልዑካን አጀንዳዎች በማቀናጀት የጋራ አጀንዳና የመወያያ ሕግ በመቅረጽ፣ ልዑካኑም እንዲስማሙበት በማድረግ፣የሰላምና አንድነት ንግግር እንዲካሄድ አድርጓል። ንግግሩም በመግባባትና በመደማመጥ ተካሂዷል።  በሁለቱም በኩል ከላካቸው አካል ይዘውት የመጡትን መሠረተ ሐሳብ በሰፊው የተነጋገሩበት ሲሆን  በኢትዮጵያ  ልዑካን በኩል የቀረበው ዋና ሐሳብ «ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደሀገራቸው ገብተው ክብራቸው ተጠብቆና የሚያስፈልጋቸው ተሟልቶላቸው እሳቸው በፈለጉት ቦታ ይኑሩ» የሚል ነው። በውጭ ሀገር  ያሉት ልዑካን ግን ቅዱስነታቸው« ከነሙሉ ሥልጣናቸው ወደመንበራቸው መመለስ አለባቸው» ብለዋል። በነዚህ መሠረተ ሐሳቦች ላይ ሁለቱም ወገኖች  ስምነት ላይ ሊደርሱ ባለመቻላቸው  ከዚህ በሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ተስማምተዋል።

1.      ልዑካኑ ልዩነት በታየባቸው ሐሳቦች ላይ  ለመወሰን  ከአቅማችን በላይ ነው ወደላከን አካል ሂደን አስረድተን እንደገና የምንጋናኝበት አራተኛ ጉባኤ ያስፈልገናል  ስለአሉ ከጥር 15- 18/2005 ዓ/ም/Jan 23-26/2012/ እንዲደረግ፤

2.    በሁለቱም በኩል ለሰላሙ እንቅፋት የሚሆነውን ማንኛቸውም ነገር እንዳይደረግ ተስማምተዋል።የሰላምና አንድነት ጉባኤውም ልዑካኑን ለሰላምና አንድነቱ መሳካት ሲባል በሁለቱም በኩል ማለትም በውጭ ባሉት በኩል ሲመተ ኤጳስ-ቆጳሳት በኢትዮጵያ ባሉት በኩል ሲመተ-ፖትርያርክ  ከእርቁ በፊት እንዳይካሄድ ጠይቋል። ልዑካኑም የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ  ቃል ገብተዋል፤

3.    አደራዳሪው የሰላምና አንድነት ጉባኤም ባለአራት ነጥብ  የመፍትሔ ሐሳብ አዘጋጅቶ ያቀረበ ሲሆን የሁለቱም ወገን ልዑካን ወደላካቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ  ቀርቦ የመፍትሔ ሐሳቡን ያቀረበው የሰላምና አንድነት ጉባኤው ልዑካንን ልኮ  ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ  ጉባኤ እንዲያስረዳ ተስማምተዋል፤

4.    በሁለቱም በኩል አስቼኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተደርጎ በጥር ለሚካሄዳው 4ኛው ጉባኤ አበው ለአድነቱ መሳካት የሚረዳ የመፍትሄ ሀሳብ ይዘው እንዲቀርቡና  አባቶችን እንዲያስረዱ ተስማምተዋል።

ልዑካኑ ስለሰላም እየተነጋገሩ ሳለ አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በVOA ልዑካኑ ከሚደራደሩበት  ርዕሰ ጉዳይ ጋር የተያያዘና  ለሰላሙ ሂደት እንቅፋት የሚሆን  መልዕክት ነው እንዴት ነው የሰላሙ ጉባኤ የሚቀጥለው በሁኔታው በጣም አዝነናል ሲሉ በውጭ ሀገር የሚኖሩት ልዑካን በመግለጻቸው የሰላምና አንድነት ጉባኤው አቃቤ መንበሩን አነጋግሮ መልስ ለመስጠት ቃል ገብቷል።

        የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በመላው ዓለምና በሀገራችን ኢትዮጵያ የሚኖሩ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ  ካህናትና ሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ  ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ወደሁለቱም  አካላት ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት  ድምጻቸውን እንዲያሰሙ፣ ለቤተ ክርስቲያኑ የማያገባው ሰው የለምና ተገቢውንም ክርስቲያናዊ ዋጋ በሚያስፈልገው ሁሉ እንዲከፍሉ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን  የሰላምና አንድነት ጉባኤ ጥሪውንም ያስተላልፋል።

ከቤተ ክርስቲያንም አንድነት በፊት  በኢትዮጵያ የፓትርያርክ ሲመት፤ በሰሜን አሜሪካም ሲመተ ኤጲስቆጶሳት እንዳይካሄድ የሰላም ጉባኤው በቤተ ክርስቲያን አምላክ ስም ሁለቱን ምፍል  ይጠቃለን።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በዳለስ እና አካባቢው ለሚገኙት አብያተክርስቲያንን ስላደረጉት አብርሃማዊ መስተንግዶ በእግዚአብሔር ስም ምስጋናውን ያቀርባል። ይልቁንም  የዳላስ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን/ ምዕመናን/ ከተጀመሮ ጀምሮ እስከመጨረሻ  ንገንዘባቸውን ጉልበታቸውንና ጊዜአቸውን የተወደደ ማሥዋእት አድርገው ስለቀረቡና ታሪክ የማይረሳው ከፍተኛ ሥራ ስለሰሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  የሰላምና አንድነት ጉባኤ ምስጋናውን  ያቀርባል።      

በመጨረሻም ለአራተኛው ጉባኤ አበው መሳካት የሰላሙን ጥረት በገንዘብ ለመርዳት የምትፈልጉ ክርስቲያኖች ሁሉ ከዚህ በሚከተለው አካውንታችን በቀጥታ ልትለግሱን ትችላላችሁ። [Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Council for Peace - Bank Of America MD 99700101 Acct. # 4460193806663] ስለ ጉባኤው ሂደትና ታሪክ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ብሎጋችንን  ይጎብኙ።

 
http://eotc-peace-and-unity.blogspot.com/
«ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር»

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አምንድነት  ጉባኤ

 

 

 

 

 

Thursday, December 6, 2012

የሰላም ድርድሩ ተጀምሯል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት የተጀመረው የሰላም ድርድር የተጀመረ ሲሆን የመጀመሪያ ቀን ውሎ ምን እንደሚመስል በሚቀጥለው መልክ አቅርበናል::የኢትዩጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትተከታዮች በሙሉ በጸሎት እንድትበረቱ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ይማጸናል::

የመጀመ ቀን ውሎ

ጠዋት

ü  መርሐ ግብር መሪ / መ/ር አንዱዓለም ዳግማዊ ከሰላምና አንድነት ጉባኤው

ü  ጸሎተ ኪዳን ተደርሷል/ብብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ መሪነት

ü  የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በመላከ መንክራት ቀሲስ አንዱዓለም ይርዳው  

ü  ከዚህ ጉባኤ ምን እንደሚጠበቅ በቆሞስ አባ ጽጌ ደገፋው  ባለ አምስት ነጥብ ማብራሪያ አቅርበዋል::

ü  የሰላምና  አንድነት ጉባኤው አባላት ትውውቅ ተደርጓል

ü  የመግቢያ መልዕክት በብፁዕ አቡነ ገሪማ  ቀርቧል

ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው እንደገለጹት ስለ ኢትዮጵያ  መጽሐፍ ቅዱስ የተናገረውን በመዘርዘር ኢትዮጵያ አገረ እግዚአብሔር መሆኗን አብራርተው ቤተ ክርስቲያን ለአገር ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ዘርዝረው በተለያዩ ጊዜዎች ፈተና  እንደገጠማትና እንደተወጣችው  አብራርተዋል::ሰላም ማምጣት  አስፈላጊ መሆኑን ና ባፋጣኝ እንዲፈጸም አስረድተዋል::   

ü  ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅም ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል

ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው ታራቂዎችም አስታራቂዎችም እኛ ነን: ብለዋል::

 
ü  ከኢትዮጵያው ሲኖዶስና ከወጪው ሲኖዶስ የቀረቡትን ሁለት የመወያያ አጀንዳዎች በማጣጣም  በሰላምና  አንድነት ጉባኤው የቀረቡት ስድስት  የዕርቀ ሰላሙ የውይይት አጀንዳዎች እና  የመወያያ ደንብ ስለማጽደቅ የሚገልፀው ጹሑፍ በንባብ በመርሐ ግብር መሪው  ተነቦ ጉባኤው አጀንዳውን አጽድቋል::
ከሰዓት በኃላ

አወያይ ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ::

ውይይቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ከሥልጣናቸው እንዴት ሊወርዱ እንደቻሉ የታሪክ ምስክርነታቸውን በወቅቱ በነበሩ ሁለቱም አባቶች ማለትም በኢትዮጵያው ሲኖዶስ ልዑካንና በውጪው ዓለም የሚገኘው ሲኖዶስ ልዑካን የታሪክ ምስክርነት ሰጥተው: ውይይቱ በሰላምና በፍቅር ቀጥሎ የዋለ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ኢትዮጵያ  መመለስ ባማስመልከት ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በይደር ተጠናቅቋል
ዝርዝሩን እንመለስበታለን
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን አንድ ያድርግልን

 

Friday, October 19, 2012

10/15/2012
ጥቅምት 5/2005ዓ/ም

ወቅታዊውን የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ አስመልክቶ የወጣ መግለጫ።

 
“ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።”
 

          ጥንታዊትና ሐዋርያዊት፣ ብሔራዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም እንደ ቀድሞው አንድነቷ ጸንቶ ልትቆም፣ ሕዝቦቿንም ልትሰበስብና በሰላምና በአንድነት ጸንተው እንዲኖሩ ተግታ ማስተማር እንድትችል መጀመሪያ በመሪዎቿ መካከል ያለውን ልዩነት በአንድነት ልትለውጠው ይገባል። ይህም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ እምነት ነው። እነሆ በዘመናችን ከሁለት ከሦስት ተከፍላ ልጆችዋም እንደ ጠላት ማዶ ለማዶ የሚተያዩበት ዘመን ሊያከትም ይገባዋል። ምክንያቱም ይህ ልዩነት የቤተ ክርስቲያኒቱን የረጅም ዘመን ታሪክና መንፈሳዊ አቋም በእጅጉ ከማዛባቱም በላይ በልጆቿም መካከል ፍቅርን እያጠፋና ኃይሏን እያዳከመ ስለሚገኝ ነው። ክፍፍሉም የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንና የሀገራችን የኢትዮጵያን አንድነት ልውና ለማይፈልጉም ትልቅ በር ከፍቶላቸዋል። በአባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት፣ ከሁለቱም አቅጣጫ የተላለፈው ውግዘት፣ በዜና አውታሮች የሚሰማውና በድረ ገጾች የሚነበበው መነቃቀፍ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች መንፈሳዊ ስሜት እጅጉን ጎድቶአል። ታላቋን ቤተ ክርስቲያን የሚያከብሩትን ኢትዮጵያውያንም አሳፍሯል፤ ይህ ያሳሰባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናንም በታላቅ ኀዘንና ጸሎት ላይ ይገኛሉ።

 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ዋና ተግባር በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች አባቶቻችን ልዩነታቸውን ለማስወገድና የቤተ ክርስቲያንን ችግር በውይይት ለመፍታት እንዲችሉ የሰላምና የአንድነት መድረክ ማመቻቸትና ችግሩ ለዘለቄታው እንዲፈታ ተግቶ መሥራት ነው።

 
የሰላምና አንድነት ጉባኤው ዓላማ፣ አቋምና ግብ እንዲሁም ያካሔዳቸው ጉባኤያት

          የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ዓላማው ቤተ ክርስቲያንን አንድ ማድረግ፣ ግቡ የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት ማየት፣ አቋሙ በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙትን አባቶች በአክብሮትና በእኩልነት በማየት ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ጠንክሮ መሥራት ነው። ይህንንም በአጽንዖት የሚገልጽ የሥራ መመሪያ አውጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል። ጉባኤው ከዚህ በፊት የመጀመሪያውን ጉባኤ አበው  ከሐምሌ 26-28, 2002 (August 2-5/2010) Hilton McLean Tysons Corner 7920 Jones Branch DR Virginia 22102 ማዘጋጀቱና በኢትዮጵያና በውጭ ሀገር በሚገኙ አባቶች መካከል የሰላም ንግግር እንዲጀመር ማድረጉ ይታወሳል። ሁለተኛውን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ደግሞ በአሪዞና ክፍለ ግዛት  ከየካቲት 2-9, 2004 /ም(February 10-17/2012) ማካሄዱ ይታወቃል። በመቀጠልም ሦስተኛውን ጉባኤ አበው በማዘጋጀት ላይ እንዳለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በድንገት በማረፋቸው ጉባኤው የተሰማውን ኃዘን ገልጿል። ከዚህም ጋር በነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም. ልዑካንን ሰይሞ ወደ አትዮጵያ በመላክ በቅዱስነታቸው አባታዊ ቡራኬና በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ንግግር ከመቼውም በበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት ፍጻሜ ስለሚያገኝበት ሁኔታ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጽሑፍና በቃል ማብራሪያ አማካይነት አቅርቦ ውይይት እንዲካሔድ በማድረግ የዕርቀ ሰላሙን ቀጣይነት ከቅዱስ ሲኖዶስ በተጻፈለት ደብዳቤ አረጋግጧል።

  
          ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወሰላመ እግዚአብሔር እንተ ኩሉ ባቲ፣ ወትትሌዓል እምኩሉ ልብ፣ ታጽንኦ  ለልብክሙ ወለህሊናክሙ በኢየሱስ ክርስቶስ” (ፊልጵ. 4፥8) ሲል የሰበካትን ሁሉ ያለባትን፣ ለሁሉ የምትጠቅም ክብረ ሥጋ፣ ክብረ ነፍስ የሚገኝባትን፤ ሕይወተ ሥጋ ወነፍስ፤ ዕርገተ ጸሎት ወመሥዋዕት የሚከናወንባትን የቤተክርስቲያንን ሰላምና አንድነት መንገድ ለመፈለግና ዕርቀ ሰላም ለመመሥረት በጥቅምት ወር በሀገር ውስጥና  በውጭ ሀገር ከሚካሔደው ጉባኤ ሲኖዶስ ወሳኝ አቋምና ሰላምን የሚያስቀድም ውሳኔ ይጠበቃል። በመሆኑም በውጭም ሆነ በውስጥ የሚኖሩ አባቶቻችን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በመላው ዓለም የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ በጉጉት የሚጠብቁትን የቤተ ክርስቲያን የአንድነት ቀን ያበሥረናል፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ለቤተ ክርስቲያናቸው ያላቸውን ፍጹም አክብሮትና ፍቅር የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በማስቀደም ያከበረቻቸውን ቤተ ክርስቲያን ለወደፊት ተለያይታ ከመቅረት ይታደጓታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

በቅርቡ ከሚካሔደው የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ መልዓተ ጉባኤ ምን ይጠበቃል?

1ኛ/ እናት ቤተ ክርስቲያንን ወደ ቀደመ ክብሯ ለመመለስ ታሪካዊ ሥራ መሥራት፤ ከራስ ክብር ይልቅ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ማስቀደም፤
 

2ኛ/ ባለፈው ችግር ላይ ጊዜን ከማጥፋት ይልቅ በመፍትሔው ላይ በማተኮር ወደፊት ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልገውን የሰላምና አንድነት መሠረት መጣል፤

3ኛ/ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት 21 ዓመታት በልዩነትና በክፍፍል ጉዞዋ በዓለም ፊት ያስመዘገበችውን አሳዛኝና አሳፋሪ የልዩነትና የክርክር ምዕራፍ ዘግቶ የሰላምና አንድነትን ዜና ማብሰር፤
 

4ኛ/ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በእርስ በእርስ ልዩነት የሚያጠፉትን ጊዜ፣ የጠፋውን በመፈለግ፣ የተበተነውን መንጋ በመሰብሰብ ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የኅብረተሰቡን የአስተሳሰብ ደረጃ የጠበቀ፣ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያንን ሁልጊዜ በመምህርነትዋ እንድትቀጥል የሚያደርግ የሊቅነት ሥራ እንዲሠሩ ለማድረግ አንድነቷና ሰላሟ የሚመለስበትን ታሪካዊ ሥራ መሥራት።

5ኛ/ ሕዝባችን ከዕለት ወደ ዕለት በአባቶቹ እያፈረና በዚህም ተነሣ ከእናት ቤተ ክርስቲያን እየራቀ እንዳይሔድ በዘመናችን የተከፈቱትን የመከፋፈልና የመወጋገዝ በሮች በመዝጋት የክርስቶስ መንጋ በሰላምና በፍቅር ወጥቶ የሚገባበት ዘለቄታዊ የሰላምና አንድነት በር እንዲከፈት የሚያደርግ ሐዋርያዊ ተግባር ከጥቅምቱ ሲኖዶስ ይጠበቃል።
 

          ከምንም በላይ ደግሞ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳውያን አባቶች እንደተወጋገዙ በሞተ ሥጋ ማለፍ ለቤተ ክርስቲያን ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ ከአባቶች የተሠወረ አይደለም። እንደሚታወቀው በርካታ አባቶቻችን  የቤተክርስቲያናቸውን የሰላምና አንድነት ቀን ሳያዩት በሞተ ሥጋ እያለፉ ነው። ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚገኙት ሊቃነ ጳጳሳት ይህን የታሪክ አጋጣሚ ተጠቅመው የቤተ ክርስቲያን ችግር  ለዘለቄታው በመፍታት የቤተክርስቲያንን የልዩነት ታሪክ እንደሚለውጡት ተስፋችን ጽኑ ነው። ስለዚህ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የምትገኙ ክቡራን አባቶቻችን ሊቃነ ጳጳሳት እግዚአብሔር የከፈተውን የሰላም በር ተጠቅማችሁ የምትሠሩት ሥራ ከታሪክ ተወቃሽነት የሚያድን ብቻ ሳይሆን በእውነት ዕርግናችሁ የክብርና የድል እንዲሆን የሚያደርግ፣ እያዘኑ ከማለፍ የሚያድን የአገልግሎታችሁ ዘውድ ላከበረቻችሁም ቤተ ክርስቲያን ለዘወትር ክብርና ሞገስ ይሆናል ብለን በእጅጉ እናምናለን።
 

በውጭ ሀገር የሚኖሩትን አባቶች በተመለከተ  

          በውጭ አገር የሚገኙት አባቶች ለተጀመረው የቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ጉዞ እንቅፋት የሚሆን ማንኛውም ዓይነት መግለጫ በቃልም ሆነ በጽሑፍ ከመስጠት እንዲቆጠቡ በታላቅ ትሕትና እንጠይቃለን።  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስንና በስደት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን ባነጋገረበት ወቅት ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ወደ ኤርትራ ያደረጉትን ጉዞ ቅዱስ ሲኖዶስ በፍጹም እንደማያውቀውና ቅዱስ ሲኖዶስንም እንደማይወክል በመግለጽ፣ ይልቁንም ብፁዕነታቸው ጉዞውንም ያደረጉት በግላቸው መሆኑን ለሰላምና አንድነት ጉባኤው በአጽንዖት አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙትን አባቶች በተመለከተ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  የሰላምና  አንድነት ጉባኤ በቅድስት አገር ኢትዮጵያ ለሚገኙት መላው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከታላቅ አደራ ጋር ማሳሰብ የሚፈልገው ዐቢይ ጉዳይ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በምትገኙት ብፁዓን አባቶች መልካም ፈቃድ የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት ከፍጻሜ ሳይደርስ በመካከል ሌላ  ፓትርያርክ ቢመረጥ ቤተ ክርስቲያናችን ለፉት ሃያ ዓመታት ተከፋፍላ ካሳለፈችው አሳፋሪና አሳዛኝ ታሪክ እጅግ ወደ ባሰና ውስብስብ ወደሆነ ችግር ውስጥ እንድትወድቅ ያደርጋታል ስለሆነም ከዚህ ፈተና ለመዳን ብቸኛው መፍትሔ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የምትገኙት ብፁዓን አባቶች በጋራ ተወያይታችሁ፣ ያለፈውን ችግር በውይይት ፈትታችሁ፤ የልዩነት ታሪካችንን በአንድነት አድሳችሁ ለወደፊቱ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይበጃል የምትሉትን ማናቸውንም መፍትሔ በጋራ ኃላፊነት ወስዳችሁ በአንድነት ተግባራዊ እንድታደርጉ በታላቅ ትሕትናና አክብሮት እንጠይቃለን። ይህ ካልሆነ ግን በአገር ውስጥም ሆነ አገር ውጪ ያሉት አባቶች ሌላ ፓትርያርክ እየሾሙ ለዘለቄታው በልዩነት እንዲኖሩ በር ከመክፈቱም በላይ ቀሪውን የአገልግሎት ዕድሜያችሁንንም በልዩነት የሚያሳልፍ በመሆኑ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስትሉ ከሁሉ አስቀድማችሁ ላለፉት ሃያ ዓመታት የቆየውን የልዩነት ምዕራፍ በፍጹም ኅብረትና አንድነት እንድትዘጉት የሰላምና አንድነት ጉባኤው በአክብሮት ይማጸናችኋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትን በተመለከተ

 እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ለሕዝባችን ሰላምና አንድነት መሠረት መሆኑ ይታመናል። ስለዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥትም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት አስመልክቶ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግና ብፁዓን አባቶችም ያለ አንዳች ጣልቃ ገብነት/ተጽእኖ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት የሚበጀውንና ተገቢውን ውሳኔ በራሳቸው እንዲያስተላልፉ መሉ ትብብር እንዲያደርግ የሰላም ጉባኤው በአጽንኦት ይጠይቃል። የቤተ ክርስቲያኒቱ መከፋፈል ለትውልድም ሆነ ለአገርም የማይበጅ በመሆኑ ለተጀመረው የዕርቀ ሰላም ሒደት ስኬታማነት ቤተ ክርስቲያንን በሚያስፈልገው ተገቢ መንገድ በማገዝና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጽእኖ ባለማድረግ ይተባበር ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።

          በመጨረሻም የቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ካህናት ወምእመናን አካላችንን ቤተ ክርስቲያንን የለያያት ችግር ለዘለቄታው ተወግዶ ፍጹም ሰላምና አንድነት እንዲሰፍንባት ዘወትር ነቅተንና ተግተን ልንጸልይ ይገባል። በመሆኑም ስለ አንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንድታሰሙ በትሕትና እንጠይቃለን።

 “ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ!”
 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  የሰላምና  አንድነት ጉባኤ።

Friday, August 17, 2012

የኃዘን መግለጫ




ነሐሴ 11/2004 ዓ/ም
Aug 17/2012

“ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር” (መዝ 115፥6)

የአምስተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ  የብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስን ዕረፍት አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  የሰላምና አንድነት ጉባኤ ጽ/ቤት የተሰጠ የኃዘን መግለጫ።

ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ

አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

እንዲሁም በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያና በመላው ዓለም ለሚኖሩ የኢትጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን በሙሉ።

          በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በአምስተኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም፤ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የዓለም የሰላም አምባሳደር ድንገተኛ ዕረፍት ምክንያት የተሰማውን ከፍተኛና ትልቅ ኃዘን ይገልጻል። እንደሚታወቀው ቅዱስነታቸው   ለቤተ ክርስቲያናችን ዕድገትና መሻሻል፣ መጠናከርና መስፋፋት የሚጠቅሙ በርካታ መንፈሳዊ ተግባራትን ያከናወኑ  ታላቅ የቤተ ክርስቲያናችን አባትና  የሥራ ሰው ነበሩ። በመሆኑም ቅዱስነታቸው በአገልግሎት ዘመናቸው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከናወኗቸው ዘርፈ ብዙ ሐዋርያዊ ተግባራት ምን ጊዜም ሕያውነታቸውን ሲያስታውሱ ይኖራሉ። ቅዱስነታቸው ብሔራዊውን የአብነት ትምህርትና ዘመናዊውን ዕውቀት አገናዝበው የተማሩ ታላቅ ሊቅ ስለነበሩ ለቤተ ክርስቲያን እጅግ አስፈላጊ ቅዱስ አባት ነበሩ፤ ይልቁንም ባለንበት ዘመን ቤተ ክርስቲያናችንን በዓለም መድረክ ወክለው ያከናወኗቸው ብዙ ሥራዎች ዘወትር ሲታሰቡ ይኖራሉ። ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን እኒህን ታላቅ አባት በድንገት በማጣቷ ልባዊ ኃዘናችንን በድጋሚ እንገልጻለን። በእውነቱ የቅዱስነታቸው  ድንገተኛ ዜና ዕረፍት ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ  ኃዘን ነው።

          ይልቁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በቅዱስነታቸው አባታዊ ቡራኬና በቅዱስነታቸው በሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መልካም ፈቃድ ሦስተኛውን ዙር የሰላምና አንድነት ጉባኤ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ሳለ ይህንን ቤተ ክርስቲያንን አንድ የሚያደርግ ታሪካዊ ሒደት ለፍጻሜ ሳይበቃ የቅዱስነታቸው ዜና ዕረፍት መስማቱ ጉባኤውን በእጅጉ አሳዝኖታል፤ ሊያስከትል የሚችለው ውጣ ውረድም ከወዲሁ አሳስቦታል። ቅዱስነታቸው የጀመሩትን የቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ጥረት የመጨረሻ ፍሬ ሳያዩ በድንገት በማለፋቸው ኃዘናችን ወሰን የለውም። የሰላምና አንድነት ጉባኤው በቅዱስነታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው የጉባኤውን የኃዘን መግለጫ የሚያደርሱ ልዑካንን  ሰይሞ ለመላክ በአንድነት ወስኗል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ቤተ ክርስቲያንን አሁን ካለችበት አሳሳቢ የልዩነት ፈተና ይበልጥ ወደ ባሰና ወደ ከፋ ችግር እንዳትሄድ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ተቀዳሚ ሥራው በማድረግ ለዘመናት በአንድነቷ ጽንታ የኖረችውን ቤተ ክርስቲያን የቀድሞ ታሪኳን ለመመለስና ለማደስ ተገቢውን ሥራ በአንድነት እንዲሠራና እስካሁን ድረስ የቆየው የልዩነት ምዕራፍ እንዲዘጋ፣ በቅዱስነታቸውና በቅዱስ ሲኖዶስ በጎ ፈቃድ የተጀመረውን የሰላምና አንድነት ሒደትም ለፍሬ ያበቃው ዘንድ ጉባኤው ከታላቅ አደራ ጋር ይማጸናል።

በመሆኑም የሰላምና አንድነት ጉባኤው ለቅዱስ ሲኖዶስና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መላው ካህናትና ምእመናን ወምእመናት ከዚህ የሚከተለውን መልእክት ያስተላልፋል።

1ኛ/ በቅዱስነታቸው ድንገተኛ ዕረፍት ምክንያት የተሰማንን ጽኑ ኃዘን እየገለጽን ከምንም በላይ በቅዱስ ሲኖዶስ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ዋነኛውና አንገብጋቢው ጉዳይ ቤተ ክርስቲያንን አንድ ማድረግ መሆኑን በአጽንኦት እንገልጻለን፤  እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ባለፈው ሐምሌ ወር ሦስተኛውን ጉባኤ አበው ለማካሄድ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነበር። ይሁን እንጂ በግንቦቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የላክነው ደብዳቤና ባለ ሰባት ነጥብ የመፍትሔ ሐሳቦች በአገር ውስጥና በውጭው ዓለም የሚገኙት አባቶቻችን በዕርቀ ሰላም ውይይቱ ላይ ለመገኘት ሙሉ ፈቃዳቸው መሆኑን ገልጸውልን ነበር። በዚህ መካከል ግን በአዲስ አበባ በኩል በሰላምና አንድነት ጉባኤው የቀረቡትን ሰባቱን የመፍትሔ ሐሳቦች አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ በወርኃ ሐምሌ መግቢያ ላይ ተነገጋሮባቸው በአፋጣኝ መልስ እንደሚሰጠን በደብዳቤ ተገልጦልን ነበር። ያንን መልካም ዜና በጉጉት እየተጠባበቅን ሳለን ይህ ድንገተኛ ኃዘን ቤተ ክርስቲያንን ገጠማት፤ አሁንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ሦስተኛውን የዕርቀ ሰላም ውይይት በወርኃ ጥቅምት ከሚካሔደው ዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በፊት ለማካሔድ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ነው። በመሆኑም በመላው ዓለም የተበተነችውን ቤተ ክርስቲያን አንድ ለማድረግ፣ በሀገር ውስጥና በሀገር ውጭ የሚገኙት አባቶችም በቅርቡ በሚዘጋጀው የሰላምና አንድነት መድረክ ተገናኝተው ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ተነጋግረው፣ ችግሩን በውይይት በመፍታት ቤተ ክርስቲያንን አንድ ያደርጓት ዘንድ ጥሪውን ያቀርባል።  

 2ኛ/ ቤተ ክርስቲያን ለወደፊቱ ተለያይታ እንዳትቀር በሀገር ውጭና ከሀገር ውስጥ ባሉት አባቶች መካከል ያለው ልዩነት በአንድነት ሳይፈታ ሌላ ፓትርያርክ የመተካቱን ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶስ ከወዲሁ በከፍተኛ አትኩሮት እንዲያስብበት፤ ይልቁንም የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት በማጽት የቀድሞውን የአንድነት ታሪክ ይመልሱት ዘንድ ጉባኤው በቤተ ክርስቲያን ስም ከልብ ይማጸናል።

3ኛ/ በዚህ አጋጣሚም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥትም ለቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚጠበቅበትን የበኩሉን አስተዋጽኦ በአግባቡ እንዲያደርግ በአክብሮት እንጠይቃለን።

4ኛ/ በመላው ዓለም ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ሊቃነ ጳጳሳት፣ ማኅበረ ካህናትና ሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን አንድ በማድረጉ ታሪካዊ ሒደት ላይ በጾም፣ በጸሎትና በሚያስፈልገው ማናቸውም ነገሮች ሁሉ ተገቢውን ድጋፍ በመስጠት ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ይሠሩ ዘንድ በትሕትና እንማጸናለን።

 በመጨረሻም አምላከ አበው እግዚአብሔር የቅዱስነታቸውን ነፍስ ከማኅበረ አበው ኄራን እንዲደምርልንና ለመላው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እንዲሁም ለቅዱስነታቸው ቤተ ሰቦች ሁሉ መጽናናትን እንዲሰጥልን ከልብ እንመኛለን።

የቅዱስነታቸው በረከት አይለየን።

የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት ያሳየን!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ።

Sunday, May 13, 2012

የሰላምና አንድነት መልእክት የሚያስፈጽሙ ልዑካንን ወደ አዲስ አበባና ወደ ሰሜን አሜሪካ ተልከዋል።

"ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን”  “ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ"

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በወርሐ ግንቦት 2004 ዓ/ም ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የቤተ ክርስቲያናችንን የሰላምና አንድነት መልእክት የሚያስፈጽሙ ልዑካንን ወደ አዲስ አበባና ወደ ሰሜን አሜሪካ  ልኳል።

 ወደ አዲስ አበባ የተላኩት መምህር አንዱ ዓለም ዳግማዊ ሲሆኑ፣ በውጭ ሀገር በዋሽንግተን ዲሲ ወደ ተካሄደው ቅ/ ሲኖዶስ ደግሞ  አባ ጽጌ ድንግል ደገፉው ፥ ሊ/ማ  ዶ/ር አማረ ካሣዬ እና መምህር ልዑለ ቃል አካሉ ተልከዋል።

ጉባኤው ልዑካኑን የላከው በአሪዞና ከተማ የተካሄደውን የሁለተኛውን ዙር ጉባኤ አበው ሪፖርት የያዘ ደብዳቤና ለአባቶችና ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም ይጠቅማሉ ብሎ ጉባኤው ያመነባቸውን ባለሰባት ነጥብ የመፍትሔ ሐሳበችን እንዲያደርሱና ከጉባኤው የሚነሱትን ጥያቄዎች ጉባኤውን ወክለው እንዲመልሱ ነው። ጉባኤው የመፍትሔ ሐሳቦቹ በሁለቱም ዘንድ ተቀባይነት ካገኙ ለቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ቀን መቃረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብሎ ያምናል።

እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን አንድ በማድረግ ሕዝቡን ያጽናና ዘንድ ጸልዩ።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ