Saturday, December 22, 2012

ከኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ጉባኤ የተሰጠ መግለጫ


      DEC. 21/2012

ታኅሣስ 12/2005 ዓ/ም

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ

የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

 

“ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።”

 

        የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በኢትዮጵያም ሆነ በሰሜን አሜሪካ ባሉት አባቶች ሙሉ ፈቃድና እውቅና አግኝቶ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ፍጹም ተግቶ የሚሠራ ኮሚቴ መሆኑ ይታመናል። ስለሆነም በቅርቡ ሰላምና አንድነት ጉባኤ አዘጋጅነት ከኅዳር 26 ቀን እስከ 30 ቀን 2005 ዓ.ም (Dec. 5-9, 2012) በዳላስ፤ ቴክሳስ የሦስተኛው ዙር ጉባኤ አበው በመልካም ሁኔታ መካሔዱ ይታወቃል። በዚህ ታሪካዊ የዕርቀ ሰላም ንግግር ላይ ከኢትዮጵያና ከአሜሪካ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተሰይመው የተላኩት ልዑካን በፍጹም መከባበር ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት በስፋት ተወያይተዋል። በውይይቱም ወቅት ሁለቱም ወገኖች ከላካቸው አካል ይዘውት የመጡትን መሠረተ ሐሳብ በሰፊው የተነጋገሩበት ሲሆን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገራቸው መመለስ ለዕርቀ ሰላሙ ስኬታማነት ዋነኛ መሠረት መሆኑን በጋራ ተስማምተዋል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ልዑካን በኩል የቀረበው ዋና ሐሳብ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ ቅድስት አገራቸው ገብተው፣ ክብራቸው ተጠብቆና የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶላቸው እርሳቸው በፈለጉት ቦታ ይኑሩ”፤ የሚል ሲሆን የዚህ ፍሬ ሐሳብ አመክንዮ ደግሞ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው ቢመለሱ ታሪክ ይፋለስብናል የሚል ነበር።

 

 

በአንጻሩ ደግሞ በውጭ አገር ያሉት ልዑካን ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ሲባል “ቅዱስነታቸው ከነሙሉ ሥልጣናቸው ወደ መንበራቸው መመለስ አለባቸው” ሲሉ አያይዘውም ፓትርያርክ እያለ ሌላ አዲስ ፓትርይርክ መሾም ነገም በቤተ ክርስቲያን ላይ ሥርዓት አልበኝነት እንዲስፋፋ ይደርጋል፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ በሕይወት እያሉ በማን አለብኝነትና በግድ የሌሽነት የሚሾመውም ሰው ፍጹም ተቀባይነት አይኖረውም፤ ይልቁንም ሹመቱ የቤተ ክርስቲያኒቱን  አንድነት ፈጽሞ ያጠፋል፣ ልዩነቱንም ያከፋዋል የሚል ነበር። ስለዚህ ልዑካኑ ልዩነት በታየባቸው መሠረታዊ ሐሳቦች ላይ አሁን በራሳችን ለመወሰን ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ሰይሞ ወደላከን አካል ተመልሰን ጉዳዩን በስፋት አስረድተን እንደገና የምንገናኝበትና የዕርቀ ሰላሙን ውይይት የመጨረሻ ምዕራፍ የምናደርስበት ቀጣይ አራተኛ ጉባኤ በቅርቡ ያስፈልገናል ሲሉ ለሰላምና አንድነት ጉባኤው ሐሳባቸውን አቅርበዋል። ጉባኤው ከልዑካኑ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት አራተኛው ጉባኤ ከጥር 16-18 ቀን 2005 ዓ.ም (Jan 23-26/2012) በሎስ አንጀለስ፤ ካሊፎርኒያ እንዲካሔድ ሐሳብ አቅርቧል፤ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ያቀረበውን ሐሳብ  የሁለቱም ወገን  ልዑካበአንድ ድምፅ ተቀብለው ተስምተውበታል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ የግራ ቀኙን ፍሬ ሐሳብ በጥሞና አዳምጦና ጉዳዩንም በጥልቀት መርምሮ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና አንድነት ሥምረት ይበጃል ብሎ ያመነበትን ባለ አራት ነጥብ የመፍትሔ ሐሳብ ለልዑካኑ በጽሑፍ አቅርቧል።

 የሰላም ልዑካኑም በንባብ የቀረበላቸውን የመፍትሔ ሐሳብ በጥሞና ካዳመጡ በኋላ እኛ ወሳኝ አካላት ባለመሆናችን በሁለታችንም በኩል በቅርቡ አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲደረግና የሰላምና አንድነት ጉባኤው ሦስት ሦስት ልዑካንን ወደ ሁለታችንም ልኮ የመፍትሔ ሐሳቦቹን ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አቅርበው እንዲያስረዱና ተገቢው የማግባባት ሥራ እንዲሠሩ እንዲደረግ በፍጹም ቅን ልቡና አስተያየታቸውን በመስጠት በወርኃ ጥር በሚካሔደው የዕርቀ ሰላም ጉባኤ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት ሲሉ ስምምነታቸውን በአጽንዖት ገልጸዋል። ከዚህም ጋር የዕርቀ ሰላሙ ድርድር ከፍጻሜ እስከሚደርስ ድረስ በሁለቱም በኩል ለሰላምና አንድነቱ ሒደት እንቅፋት የሚሆኑ ማናቸውንም ድርጊቶች ከመፈጸም በተለይም ደግሞ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳትና ሢመተ ፓትርያርክን የመሰሉ ተግባራትን ከማከናወን እንዲቆጠቡና በትዕግሥት እንዲጠብቁ በጋራ ተማምነውና ተስማምተው በፊርማቸው አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ያሉት አባቶች ሰይመው የላኳቸው የሰላም ልዑካን እንኳን ገና ወደ ኢትዮጵያ ሳይመለሱ፣ የዕርቀ ሰላሙን ውይይት ሪፖርት ሳያቀርቡና በቀጣዩ ጉባኤ አበው ላይ በጋራ የሚመከርባቸውን ዐበይት ጉዳዮች ሳያቀርቡ ኃላፊነት በማይሰማቸውን የመንጋው እንባና ጩኸት በማይገዳቸው ጥቂት የሲኖዶስ አባላት ግፊት አስመራጭ ኮሚቴ መሰየሙ ከትናንት በስቲያ በመሰማቱ የሰላሙ ሒደት ከፍተኛ እንቅፋት ገጥሞታል። የቤተ ክርስቲያን የአንድነት ተስፋም እንዲጨልም እየተደረገ በመሆኑ በእጅጉ አዝነናል።

 የሰላምና አንድነት ጉባኤውን የሦስት ዓመት ጥረት ዋጋ ለማሳጣት  ጥረት በሚደርጉ ጥቂት የቅ/ሲኖዶስ አባላት ጉባኤው በእጅጉ አዝኗል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በእኒህ ጥቂት ግለሰቦች አማካይነት አባቶች ቤተ ክርስቲያንን ወደከፋና መፍትሔ ወደማይገኝለት ችግር እዳያስገቧት ከፍተኛ ሥጋት አድሮበታል። ይልቁንም የቤተ ክርስቲያንን የሰላምና የአንድነት በር ለመዝጋት ከመጣደፍ  እንዲታገሡና ወደማስተዋል እንዲመለሱ በቤተ ክርስቲያን አምላክ ስም በአጽንዖት እናሳስባቸዋለን። ይልቁንም የሀያ ዓመታቱ የልዩነት ችግሩ ሳይፈታ ሌላ ፓትርያርክ መሾም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንንና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትንና በመላው ዓለም የሚገኙትን ኦርቶዶክሳውያን ካህናት፣ ምእመንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን የመከራ ቀን ማራዘምና የክርስቶስን መንጋ ከመበተን ያለፈ አንዳችም ፋይዳ እንደማይኖረው እየታወቀ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚለው ኢቀኖናዊ አመለካከት ሊታሰብበት ይገባል። ስለሆነም ሰላምና አንድነት የራበው፣ ፍቅርና መተሳሰብ የጠማው፣ መለያየት የሰለቸው መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድምፁን አሰምቶ እያለቀሰና እየጮኸ በማን ላይና ለማንስ ነው አባት የሚሾመው! አሁንም አባቶች የሕዝባቸውን ድምፅ በማስተዋል እንዲሰሙ በአጽንኦት እንጠይቃለን።

በመሠረቱ ሰላምና አንድነት የማንንም ክብርና ታሪክ አያጎድፍም፤ ይልቁንም የአባቶችን ሕልውናና ክብር የሚሽረው ሕያው ታሪካቸውንም የሚያጠፋው ሰላም ባጣችና በተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖር ነው። በመሆኑም አባቶቻችን ላከበረቻቸው ቤተ ክርስቲያን ዋጋ ሊከፍሉ፣ ለአንድነቷና ለክብሯ ፍጹም ጸንተው ሊቆሙና ስለ ነገውም ትውልድ ሊያስቡ ሲገባቸው አለመታደል ሆነና እያየንና እየሰማን ያለነው ግን የተገላቢጦሽ ነው። “የአባቶችን ልጅ ለልጆች፥ የልጆችን ልብ ለአባቶች” ተብሏልና። አባቶች አደራቸውን ለመወጣት ጥረት ሊያደርጉና ለቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም ተግተው ሊሠሩ ሲገባ የቤተ ክርስቲያንን የሰላምና አንድነት በር ለመዝጋት የሚተጉ ጥቂት ሊቃነ ጳጳሳት ታላቋን ቤተ ክርስቲያን ወደ ከፋ የችግር አዘቅት ውስጥ ለማስገባት ሲታገሉ ማየት ለቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ በእጅጉ የሚያሳፍር ሆኗል። የሊቃነ ጳጳሳቱንም የአመራር ብቃትና የቅዱስ ሲኖዶስን አርቆ አሳቢነትም ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል።

ጥንታዊት ሐዋርያዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዘመናችን በታላቅ ፈተና ላይ ናት። ላለፉት 21 ዓመታት ያንገላት ልዩነት እንዲወገድና ለዘለዓለም በአንድነቷ እድትጸና ማድረግ ሲገባ ልዩነቱ ህልውናዋን እንዲፈታተን  የሚያደርግ ተግባር እየተካሄደ በመሆኑ ሁላችንም ስለቤተ ክርስቲያናችን ዝም ልንል አይገባም፣ ልዩነት ሰልችቶናል፣ አባቶቻችው እንተወጋገዙና ሕዝባቸውን እንደበተኑ ሲያልፉ ማየት ሰልችቶናል፤ የተከፋፈለችን ቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን አላወረሱንም፤  እኛም የተለያየች ቤተ ክርስቲያንን ለትውልድ ልናስተላልፍ አይገባም እንላለን። ከ40 ሚሊዮን በላይ የሁነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ሕዝበ ክርስቲያን በጥቂት አባቶች አለመግባባት ምክንያት ለልዩነትና ለሰላም እጦት ሊጋለጥ አይገባውም፤ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያኑ  ጉዳይ የማይመለከተው የቤተ ክርስቲያን ልጅ የለምና በመላው ዓለም ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት፣ካህናት፣ ሕዝበ ክርስቲያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችናሁሉ፣ እንዲሁም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ከዚህ የሚከተለውን መልክታችንን  በአክብሮት እናስተላልፋለን።

 

1)     የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድት ጉባኤ ባቀረበው የመፍትሔ ሐሳብ መሠረት ሁለቱም  አካላት መክረውና ተስማምተው ቤተ ክርስቲያንን እንድ እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

2)     ቤተ ክርስቲያንን ከፋፋሎ ለማስቀረት የሰላምንና አንድነትን በር ለመዝጋት የሚደረገው ማምንኛውም ሩጫ ተገቶ፣ አባቶች ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ሥራ እንዲሰሩ  እንጠይቃለን።

3)   በመልካም ሂደት ላይ የሚገኘው የእርቀ ሰላም ድርድር ለፍጻሜ ሳይበቃ ስድስተኛ ፓትርያሪክ ለመሾም መዘጋጀት ቤተ ክርስቲያንን ለዘለዓለም  እንደ ተለያየች እድትቀር የሚያደርግ በመሆኑ ድርጊቱ እንዲቆም በእንባና በጸሎት ሰላምን በሚጠባብቀው ሕዝብ ስም በአጽንኦት እንጠይቃለን፤ 

4)   ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነትና ሲባል መንግሥትም ባለው ኃላፊነት የዕርቀሰላሙ ድርድር ለፍጻሜ እንዲደርስ ይተባበር ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን፤

5)    በመላው ዓለም የሚገኙ ካህናትና ምዕመናን በማንቸውም ሰለማዊ መንገድ  ስለቤተ ክርስቲያን አንድነት ድምጻቸውን እንዲያሰሙ፤ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድትም ተገቢውን ሁሉ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።

6)   የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ድርድር ፍጻሜ ላይ እንዲደርስ በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም የሚገኙ ካህናትና ምዕመናን  ጸሎተ ምህላ በያሉበት እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እስተላልፋለን።

«ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን፤ስለቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ»

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ

Wednesday, December 12, 2012

የ3ኛው ጉባኤ አበው የኢ ኦ ተ ቤ ክ የሰላምና አንድነት ጉባባኤ መግለጫ



 

 
  ኅዳር30/2005 /
12/9/2012

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ሦስተኛውን  ጉባኤ አበው አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ።

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ  ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ አዘጋጅነት በዳላስ ቴክሳስ ክፍለ ግዛት ከኅዳር 25-30/2005 ዓ/ም በሚካሄደው ጉባኤ ለመገኘት ከሀገራችን ኢትዮጵያ የመጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ  ልዑካንና   በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ በስደት ላይ ከሚገኘው  የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ  ቅ/ሲኖዶስ  ልዑካን በተገኙበት 3ኛውን ዙር ንግግር አካሂዷል።  የጉባኤው ዋና ዓላማም ላለፉት 21 ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን ይከፋፈላትን ችግር ለመፍታትና አንደነቷን ለመመለስ ሲሆን በጉባኤው ላይ የተገኙ ልዑካንም፦

ከኢትዮጵያ

1.     ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ

2.    ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ሊቀ ጳጳስ

3.    ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሊቀ ጳጳስ

4.    ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሓ

      ከሰሜን አሜሪካና አውሮፓ

1.     ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ሊቀጳጳስ

2.    ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ሊቀጳጳስ

3.    ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሊቀጳጳስ

4.    ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ናቸው 

የሰላምና አንድነት ጉባኤው  የሁለቱን  ልዑካን አጀንዳዎች በማቀናጀት የጋራ አጀንዳና የመወያያ ሕግ በመቅረጽ፣ ልዑካኑም እንዲስማሙበት በማድረግ፣የሰላምና አንድነት ንግግር እንዲካሄድ አድርጓል። ንግግሩም በመግባባትና በመደማመጥ ተካሂዷል።  በሁለቱም በኩል ከላካቸው አካል ይዘውት የመጡትን መሠረተ ሐሳብ በሰፊው የተነጋገሩበት ሲሆን  በኢትዮጵያ  ልዑካን በኩል የቀረበው ዋና ሐሳብ «ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደሀገራቸው ገብተው ክብራቸው ተጠብቆና የሚያስፈልጋቸው ተሟልቶላቸው እሳቸው በፈለጉት ቦታ ይኑሩ» የሚል ነው። በውጭ ሀገር  ያሉት ልዑካን ግን ቅዱስነታቸው« ከነሙሉ ሥልጣናቸው ወደመንበራቸው መመለስ አለባቸው» ብለዋል። በነዚህ መሠረተ ሐሳቦች ላይ ሁለቱም ወገኖች  ስምነት ላይ ሊደርሱ ባለመቻላቸው  ከዚህ በሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ተስማምተዋል።

1.      ልዑካኑ ልዩነት በታየባቸው ሐሳቦች ላይ  ለመወሰን  ከአቅማችን በላይ ነው ወደላከን አካል ሂደን አስረድተን እንደገና የምንጋናኝበት አራተኛ ጉባኤ ያስፈልገናል  ስለአሉ ከጥር 15- 18/2005 ዓ/ም/Jan 23-26/2012/ እንዲደረግ፤

2.    በሁለቱም በኩል ለሰላሙ እንቅፋት የሚሆነውን ማንኛቸውም ነገር እንዳይደረግ ተስማምተዋል።የሰላምና አንድነት ጉባኤውም ልዑካኑን ለሰላምና አንድነቱ መሳካት ሲባል በሁለቱም በኩል ማለትም በውጭ ባሉት በኩል ሲመተ ኤጳስ-ቆጳሳት በኢትዮጵያ ባሉት በኩል ሲመተ-ፖትርያርክ  ከእርቁ በፊት እንዳይካሄድ ጠይቋል። ልዑካኑም የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ  ቃል ገብተዋል፤

3.    አደራዳሪው የሰላምና አንድነት ጉባኤም ባለአራት ነጥብ  የመፍትሔ ሐሳብ አዘጋጅቶ ያቀረበ ሲሆን የሁለቱም ወገን ልዑካን ወደላካቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ  ቀርቦ የመፍትሔ ሐሳቡን ያቀረበው የሰላምና አንድነት ጉባኤው ልዑካንን ልኮ  ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ  ጉባኤ እንዲያስረዳ ተስማምተዋል፤

4.    በሁለቱም በኩል አስቼኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተደርጎ በጥር ለሚካሄዳው 4ኛው ጉባኤ አበው ለአድነቱ መሳካት የሚረዳ የመፍትሄ ሀሳብ ይዘው እንዲቀርቡና  አባቶችን እንዲያስረዱ ተስማምተዋል።

ልዑካኑ ስለሰላም እየተነጋገሩ ሳለ አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በVOA ልዑካኑ ከሚደራደሩበት  ርዕሰ ጉዳይ ጋር የተያያዘና  ለሰላሙ ሂደት እንቅፋት የሚሆን  መልዕክት ነው እንዴት ነው የሰላሙ ጉባኤ የሚቀጥለው በሁኔታው በጣም አዝነናል ሲሉ በውጭ ሀገር የሚኖሩት ልዑካን በመግለጻቸው የሰላምና አንድነት ጉባኤው አቃቤ መንበሩን አነጋግሮ መልስ ለመስጠት ቃል ገብቷል።

        የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በመላው ዓለምና በሀገራችን ኢትዮጵያ የሚኖሩ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ  ካህናትና ሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ  ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ወደሁለቱም  አካላት ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት  ድምጻቸውን እንዲያሰሙ፣ ለቤተ ክርስቲያኑ የማያገባው ሰው የለምና ተገቢውንም ክርስቲያናዊ ዋጋ በሚያስፈልገው ሁሉ እንዲከፍሉ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን  የሰላምና አንድነት ጉባኤ ጥሪውንም ያስተላልፋል።

ከቤተ ክርስቲያንም አንድነት በፊት  በኢትዮጵያ የፓትርያርክ ሲመት፤ በሰሜን አሜሪካም ሲመተ ኤጲስቆጶሳት እንዳይካሄድ የሰላም ጉባኤው በቤተ ክርስቲያን አምላክ ስም ሁለቱን ምፍል  ይጠቃለን።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በዳለስ እና አካባቢው ለሚገኙት አብያተክርስቲያንን ስላደረጉት አብርሃማዊ መስተንግዶ በእግዚአብሔር ስም ምስጋናውን ያቀርባል። ይልቁንም  የዳላስ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን/ ምዕመናን/ ከተጀመሮ ጀምሮ እስከመጨረሻ  ንገንዘባቸውን ጉልበታቸውንና ጊዜአቸውን የተወደደ ማሥዋእት አድርገው ስለቀረቡና ታሪክ የማይረሳው ከፍተኛ ሥራ ስለሰሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  የሰላምና አንድነት ጉባኤ ምስጋናውን  ያቀርባል።      

በመጨረሻም ለአራተኛው ጉባኤ አበው መሳካት የሰላሙን ጥረት በገንዘብ ለመርዳት የምትፈልጉ ክርስቲያኖች ሁሉ ከዚህ በሚከተለው አካውንታችን በቀጥታ ልትለግሱን ትችላላችሁ። [Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Council for Peace - Bank Of America MD 99700101 Acct. # 4460193806663] ስለ ጉባኤው ሂደትና ታሪክ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ብሎጋችንን  ይጎብኙ።

 
http://eotc-peace-and-unity.blogspot.com/
«ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር»

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አምንድነት  ጉባኤ

 

 

 

 

 

Thursday, December 6, 2012

የሰላም ድርድሩ ተጀምሯል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት የተጀመረው የሰላም ድርድር የተጀመረ ሲሆን የመጀመሪያ ቀን ውሎ ምን እንደሚመስል በሚቀጥለው መልክ አቅርበናል::የኢትዩጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትተከታዮች በሙሉ በጸሎት እንድትበረቱ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ይማጸናል::

የመጀመ ቀን ውሎ

ጠዋት

ü  መርሐ ግብር መሪ / መ/ር አንዱዓለም ዳግማዊ ከሰላምና አንድነት ጉባኤው

ü  ጸሎተ ኪዳን ተደርሷል/ብብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ መሪነት

ü  የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በመላከ መንክራት ቀሲስ አንዱዓለም ይርዳው  

ü  ከዚህ ጉባኤ ምን እንደሚጠበቅ በቆሞስ አባ ጽጌ ደገፋው  ባለ አምስት ነጥብ ማብራሪያ አቅርበዋል::

ü  የሰላምና  አንድነት ጉባኤው አባላት ትውውቅ ተደርጓል

ü  የመግቢያ መልዕክት በብፁዕ አቡነ ገሪማ  ቀርቧል

ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው እንደገለጹት ስለ ኢትዮጵያ  መጽሐፍ ቅዱስ የተናገረውን በመዘርዘር ኢትዮጵያ አገረ እግዚአብሔር መሆኗን አብራርተው ቤተ ክርስቲያን ለአገር ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ዘርዝረው በተለያዩ ጊዜዎች ፈተና  እንደገጠማትና እንደተወጣችው  አብራርተዋል::ሰላም ማምጣት  አስፈላጊ መሆኑን ና ባፋጣኝ እንዲፈጸም አስረድተዋል::   

ü  ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅም ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፈዋል

ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው ታራቂዎችም አስታራቂዎችም እኛ ነን: ብለዋል::

 
ü  ከኢትዮጵያው ሲኖዶስና ከወጪው ሲኖዶስ የቀረቡትን ሁለት የመወያያ አጀንዳዎች በማጣጣም  በሰላምና  አንድነት ጉባኤው የቀረቡት ስድስት  የዕርቀ ሰላሙ የውይይት አጀንዳዎች እና  የመወያያ ደንብ ስለማጽደቅ የሚገልፀው ጹሑፍ በንባብ በመርሐ ግብር መሪው  ተነቦ ጉባኤው አጀንዳውን አጽድቋል::
ከሰዓት በኃላ

አወያይ ሊቀ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዓለማየሁ::

ውይይቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ከሥልጣናቸው እንዴት ሊወርዱ እንደቻሉ የታሪክ ምስክርነታቸውን በወቅቱ በነበሩ ሁለቱም አባቶች ማለትም በኢትዮጵያው ሲኖዶስ ልዑካንና በውጪው ዓለም የሚገኘው ሲኖዶስ ልዑካን የታሪክ ምስክርነት ሰጥተው: ውይይቱ በሰላምና በፍቅር ቀጥሎ የዋለ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ወደ ኢትዮጵያ  መመለስ ባማስመልከት ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በይደር ተጠናቅቋል
ዝርዝሩን እንመለስበታለን
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን አንድ ያድርግልን

 

Friday, October 19, 2012

10/15/2012
ጥቅምት 5/2005ዓ/ም

ወቅታዊውን የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ አስመልክቶ የወጣ መግለጫ።

 
“ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፤ በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።”
 

          ጥንታዊትና ሐዋርያዊት፣ ብሔራዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም እንደ ቀድሞው አንድነቷ ጸንቶ ልትቆም፣ ሕዝቦቿንም ልትሰበስብና በሰላምና በአንድነት ጸንተው እንዲኖሩ ተግታ ማስተማር እንድትችል መጀመሪያ በመሪዎቿ መካከል ያለውን ልዩነት በአንድነት ልትለውጠው ይገባል። ይህም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ እምነት ነው። እነሆ በዘመናችን ከሁለት ከሦስት ተከፍላ ልጆችዋም እንደ ጠላት ማዶ ለማዶ የሚተያዩበት ዘመን ሊያከትም ይገባዋል። ምክንያቱም ይህ ልዩነት የቤተ ክርስቲያኒቱን የረጅም ዘመን ታሪክና መንፈሳዊ አቋም በእጅጉ ከማዛባቱም በላይ በልጆቿም መካከል ፍቅርን እያጠፋና ኃይሏን እያዳከመ ስለሚገኝ ነው። ክፍፍሉም የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንና የሀገራችን የኢትዮጵያን አንድነት ልውና ለማይፈልጉም ትልቅ በር ከፍቶላቸዋል። በአባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት፣ ከሁለቱም አቅጣጫ የተላለፈው ውግዘት፣ በዜና አውታሮች የሚሰማውና በድረ ገጾች የሚነበበው መነቃቀፍ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች መንፈሳዊ ስሜት እጅጉን ጎድቶአል። ታላቋን ቤተ ክርስቲያን የሚያከብሩትን ኢትዮጵያውያንም አሳፍሯል፤ ይህ ያሳሰባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናንም በታላቅ ኀዘንና ጸሎት ላይ ይገኛሉ።

 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ዋና ተግባር በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች አባቶቻችን ልዩነታቸውን ለማስወገድና የቤተ ክርስቲያንን ችግር በውይይት ለመፍታት እንዲችሉ የሰላምና የአንድነት መድረክ ማመቻቸትና ችግሩ ለዘለቄታው እንዲፈታ ተግቶ መሥራት ነው።

 
የሰላምና አንድነት ጉባኤው ዓላማ፣ አቋምና ግብ እንዲሁም ያካሔዳቸው ጉባኤያት

          የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ዓላማው ቤተ ክርስቲያንን አንድ ማድረግ፣ ግቡ የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት ማየት፣ አቋሙ በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙትን አባቶች በአክብሮትና በእኩልነት በማየት ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ጠንክሮ መሥራት ነው። ይህንንም በአጽንዖት የሚገልጽ የሥራ መመሪያ አውጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል። ጉባኤው ከዚህ በፊት የመጀመሪያውን ጉባኤ አበው  ከሐምሌ 26-28, 2002 (August 2-5/2010) Hilton McLean Tysons Corner 7920 Jones Branch DR Virginia 22102 ማዘጋጀቱና በኢትዮጵያና በውጭ ሀገር በሚገኙ አባቶች መካከል የሰላም ንግግር እንዲጀመር ማድረጉ ይታወሳል። ሁለተኛውን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ደግሞ በአሪዞና ክፍለ ግዛት  ከየካቲት 2-9, 2004 /ም(February 10-17/2012) ማካሄዱ ይታወቃል። በመቀጠልም ሦስተኛውን ጉባኤ አበው በማዘጋጀት ላይ እንዳለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በድንገት በማረፋቸው ጉባኤው የተሰማውን ኃዘን ገልጿል። ከዚህም ጋር በነሐሴ ወር 2004 ዓ.ም. ልዑካንን ሰይሞ ወደ አትዮጵያ በመላክ በቅዱስነታቸው አባታዊ ቡራኬና በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ንግግር ከመቼውም በበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት ፍጻሜ ስለሚያገኝበት ሁኔታ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጽሑፍና በቃል ማብራሪያ አማካይነት አቅርቦ ውይይት እንዲካሔድ በማድረግ የዕርቀ ሰላሙን ቀጣይነት ከቅዱስ ሲኖዶስ በተጻፈለት ደብዳቤ አረጋግጧል።

  
          ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወሰላመ እግዚአብሔር እንተ ኩሉ ባቲ፣ ወትትሌዓል እምኩሉ ልብ፣ ታጽንኦ  ለልብክሙ ወለህሊናክሙ በኢየሱስ ክርስቶስ” (ፊልጵ. 4፥8) ሲል የሰበካትን ሁሉ ያለባትን፣ ለሁሉ የምትጠቅም ክብረ ሥጋ፣ ክብረ ነፍስ የሚገኝባትን፤ ሕይወተ ሥጋ ወነፍስ፤ ዕርገተ ጸሎት ወመሥዋዕት የሚከናወንባትን የቤተክርስቲያንን ሰላምና አንድነት መንገድ ለመፈለግና ዕርቀ ሰላም ለመመሥረት በጥቅምት ወር በሀገር ውስጥና  በውጭ ሀገር ከሚካሔደው ጉባኤ ሲኖዶስ ወሳኝ አቋምና ሰላምን የሚያስቀድም ውሳኔ ይጠበቃል። በመሆኑም በውጭም ሆነ በውስጥ የሚኖሩ አባቶቻችን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በመላው ዓለም የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ በጉጉት የሚጠብቁትን የቤተ ክርስቲያን የአንድነት ቀን ያበሥረናል፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ለቤተ ክርስቲያናቸው ያላቸውን ፍጹም አክብሮትና ፍቅር የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በማስቀደም ያከበረቻቸውን ቤተ ክርስቲያን ለወደፊት ተለያይታ ከመቅረት ይታደጓታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

በቅርቡ ከሚካሔደው የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ መልዓተ ጉባኤ ምን ይጠበቃል?

1ኛ/ እናት ቤተ ክርስቲያንን ወደ ቀደመ ክብሯ ለመመለስ ታሪካዊ ሥራ መሥራት፤ ከራስ ክብር ይልቅ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ማስቀደም፤
 

2ኛ/ ባለፈው ችግር ላይ ጊዜን ከማጥፋት ይልቅ በመፍትሔው ላይ በማተኮር ወደፊት ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልገውን የሰላምና አንድነት መሠረት መጣል፤

3ኛ/ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት 21 ዓመታት በልዩነትና በክፍፍል ጉዞዋ በዓለም ፊት ያስመዘገበችውን አሳዛኝና አሳፋሪ የልዩነትና የክርክር ምዕራፍ ዘግቶ የሰላምና አንድነትን ዜና ማብሰር፤
 

4ኛ/ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በእርስ በእርስ ልዩነት የሚያጠፉትን ጊዜ፣ የጠፋውን በመፈለግ፣ የተበተነውን መንጋ በመሰብሰብ ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የኅብረተሰቡን የአስተሳሰብ ደረጃ የጠበቀ፣ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያንን ሁልጊዜ በመምህርነትዋ እንድትቀጥል የሚያደርግ የሊቅነት ሥራ እንዲሠሩ ለማድረግ አንድነቷና ሰላሟ የሚመለስበትን ታሪካዊ ሥራ መሥራት።

5ኛ/ ሕዝባችን ከዕለት ወደ ዕለት በአባቶቹ እያፈረና በዚህም ተነሣ ከእናት ቤተ ክርስቲያን እየራቀ እንዳይሔድ በዘመናችን የተከፈቱትን የመከፋፈልና የመወጋገዝ በሮች በመዝጋት የክርስቶስ መንጋ በሰላምና በፍቅር ወጥቶ የሚገባበት ዘለቄታዊ የሰላምና አንድነት በር እንዲከፈት የሚያደርግ ሐዋርያዊ ተግባር ከጥቅምቱ ሲኖዶስ ይጠበቃል።
 

          ከምንም በላይ ደግሞ የአንዲት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳውያን አባቶች እንደተወጋገዙ በሞተ ሥጋ ማለፍ ለቤተ ክርስቲያን ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ ከአባቶች የተሠወረ አይደለም። እንደሚታወቀው በርካታ አባቶቻችን  የቤተክርስቲያናቸውን የሰላምና አንድነት ቀን ሳያዩት በሞተ ሥጋ እያለፉ ነው። ስለሆነም በአሁኑ ሰዓት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የሚገኙት ሊቃነ ጳጳሳት ይህን የታሪክ አጋጣሚ ተጠቅመው የቤተ ክርስቲያን ችግር  ለዘለቄታው በመፍታት የቤተክርስቲያንን የልዩነት ታሪክ እንደሚለውጡት ተስፋችን ጽኑ ነው። ስለዚህ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የምትገኙ ክቡራን አባቶቻችን ሊቃነ ጳጳሳት እግዚአብሔር የከፈተውን የሰላም በር ተጠቅማችሁ የምትሠሩት ሥራ ከታሪክ ተወቃሽነት የሚያድን ብቻ ሳይሆን በእውነት ዕርግናችሁ የክብርና የድል እንዲሆን የሚያደርግ፣ እያዘኑ ከማለፍ የሚያድን የአገልግሎታችሁ ዘውድ ላከበረቻችሁም ቤተ ክርስቲያን ለዘወትር ክብርና ሞገስ ይሆናል ብለን በእጅጉ እናምናለን።
 

በውጭ ሀገር የሚኖሩትን አባቶች በተመለከተ  

          በውጭ አገር የሚገኙት አባቶች ለተጀመረው የቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ጉዞ እንቅፋት የሚሆን ማንኛውም ዓይነት መግለጫ በቃልም ሆነ በጽሑፍ ከመስጠት እንዲቆጠቡ በታላቅ ትሕትና እንጠይቃለን።  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስንና በስደት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን ባነጋገረበት ወቅት ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ ወደ ኤርትራ ያደረጉትን ጉዞ ቅዱስ ሲኖዶስ በፍጹም እንደማያውቀውና ቅዱስ ሲኖዶስንም እንደማይወክል በመግለጽ፣ ይልቁንም ብፁዕነታቸው ጉዞውንም ያደረጉት በግላቸው መሆኑን ለሰላምና አንድነት ጉባኤው በአጽንዖት አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙትን አባቶች በተመለከተ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  የሰላምና  አንድነት ጉባኤ በቅድስት አገር ኢትዮጵያ ለሚገኙት መላው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከታላቅ አደራ ጋር ማሳሰብ የሚፈልገው ዐቢይ ጉዳይ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ በምትገኙት ብፁዓን አባቶች መልካም ፈቃድ የተጀመረው የዕርቀ ሰላም ውይይት ከፍጻሜ ሳይደርስ በመካከል ሌላ  ፓትርያርክ ቢመረጥ ቤተ ክርስቲያናችን ለፉት ሃያ ዓመታት ተከፋፍላ ካሳለፈችው አሳፋሪና አሳዛኝ ታሪክ እጅግ ወደ ባሰና ውስብስብ ወደሆነ ችግር ውስጥ እንድትወድቅ ያደርጋታል ስለሆነም ከዚህ ፈተና ለመዳን ብቸኛው መፍትሔ በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የምትገኙት ብፁዓን አባቶች በጋራ ተወያይታችሁ፣ ያለፈውን ችግር በውይይት ፈትታችሁ፤ የልዩነት ታሪካችንን በአንድነት አድሳችሁ ለወደፊቱ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይበጃል የምትሉትን ማናቸውንም መፍትሔ በጋራ ኃላፊነት ወስዳችሁ በአንድነት ተግባራዊ እንድታደርጉ በታላቅ ትሕትናና አክብሮት እንጠይቃለን። ይህ ካልሆነ ግን በአገር ውስጥም ሆነ አገር ውጪ ያሉት አባቶች ሌላ ፓትርያርክ እየሾሙ ለዘለቄታው በልዩነት እንዲኖሩ በር ከመክፈቱም በላይ ቀሪውን የአገልግሎት ዕድሜያችሁንንም በልዩነት የሚያሳልፍ በመሆኑ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስትሉ ከሁሉ አስቀድማችሁ ላለፉት ሃያ ዓመታት የቆየውን የልዩነት ምዕራፍ በፍጹም ኅብረትና አንድነት እንድትዘጉት የሰላምና አንድነት ጉባኤው በአክብሮት ይማጸናችኋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትን በተመለከተ

 እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ለሕዝባችን ሰላምና አንድነት መሠረት መሆኑ ይታመናል። ስለዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥትም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሰላምና አንድነት አስመልክቶ አስፈላጊውን ትብብር በማድረግና ብፁዓን አባቶችም ያለ አንዳች ጣልቃ ገብነት/ተጽእኖ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት የሚበጀውንና ተገቢውን ውሳኔ በራሳቸው እንዲያስተላልፉ መሉ ትብብር እንዲያደርግ የሰላም ጉባኤው በአጽንኦት ይጠይቃል። የቤተ ክርስቲያኒቱ መከፋፈል ለትውልድም ሆነ ለአገርም የማይበጅ በመሆኑ ለተጀመረው የዕርቀ ሰላም ሒደት ስኬታማነት ቤተ ክርስቲያንን በሚያስፈልገው ተገቢ መንገድ በማገዝና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጽእኖ ባለማድረግ ይተባበር ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።

          በመጨረሻም የቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ካህናት ወምእመናን አካላችንን ቤተ ክርስቲያንን የለያያት ችግር ለዘለቄታው ተወግዶ ፍጹም ሰላምና አንድነት እንዲሰፍንባት ዘወትር ነቅተንና ተግተን ልንጸልይ ይገባል። በመሆኑም ስለ አንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንድታሰሙ በትሕትና እንጠይቃለን።

 “ጸልዩ በእንተ ሰላመ ቤተ ክርስቲያን፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላም ጸልዩ!”
 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  የሰላምና  አንድነት ጉባኤ።