Wednesday, December 12, 2012

የ3ኛው ጉባኤ አበው የኢ ኦ ተ ቤ ክ የሰላምና አንድነት ጉባባኤ መግለጫ



 

 
  ኅዳር30/2005 /
12/9/2012

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ሦስተኛውን  ጉባኤ አበው አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ።

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ  ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ አዘጋጅነት በዳላስ ቴክሳስ ክፍለ ግዛት ከኅዳር 25-30/2005 ዓ/ም በሚካሄደው ጉባኤ ለመገኘት ከሀገራችን ኢትዮጵያ የመጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ  ልዑካንና   በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ በስደት ላይ ከሚገኘው  የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ  ቅ/ሲኖዶስ  ልዑካን በተገኙበት 3ኛውን ዙር ንግግር አካሂዷል።  የጉባኤው ዋና ዓላማም ላለፉት 21 ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን ይከፋፈላትን ችግር ለመፍታትና አንደነቷን ለመመለስ ሲሆን በጉባኤው ላይ የተገኙ ልዑካንም፦

ከኢትዮጵያ

1.     ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገሪማ ሊቀ ጳጳስ

2.    ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ሊቀ ጳጳስ

3.    ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሊቀ ጳጳስ

4.    ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሓ

      ከሰሜን አሜሪካና አውሮፓ

1.     ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ሊቀጳጳስ

2.    ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ሊቀጳጳስ

3.    ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሊቀጳጳስ

4.    ሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ ናቸው 

የሰላምና አንድነት ጉባኤው  የሁለቱን  ልዑካን አጀንዳዎች በማቀናጀት የጋራ አጀንዳና የመወያያ ሕግ በመቅረጽ፣ ልዑካኑም እንዲስማሙበት በማድረግ፣የሰላምና አንድነት ንግግር እንዲካሄድ አድርጓል። ንግግሩም በመግባባትና በመደማመጥ ተካሂዷል።  በሁለቱም በኩል ከላካቸው አካል ይዘውት የመጡትን መሠረተ ሐሳብ በሰፊው የተነጋገሩበት ሲሆን  በኢትዮጵያ  ልዑካን በኩል የቀረበው ዋና ሐሳብ «ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደሀገራቸው ገብተው ክብራቸው ተጠብቆና የሚያስፈልጋቸው ተሟልቶላቸው እሳቸው በፈለጉት ቦታ ይኑሩ» የሚል ነው። በውጭ ሀገር  ያሉት ልዑካን ግን ቅዱስነታቸው« ከነሙሉ ሥልጣናቸው ወደመንበራቸው መመለስ አለባቸው» ብለዋል። በነዚህ መሠረተ ሐሳቦች ላይ ሁለቱም ወገኖች  ስምነት ላይ ሊደርሱ ባለመቻላቸው  ከዚህ በሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ተስማምተዋል።

1.      ልዑካኑ ልዩነት በታየባቸው ሐሳቦች ላይ  ለመወሰን  ከአቅማችን በላይ ነው ወደላከን አካል ሂደን አስረድተን እንደገና የምንጋናኝበት አራተኛ ጉባኤ ያስፈልገናል  ስለአሉ ከጥር 15- 18/2005 ዓ/ም/Jan 23-26/2012/ እንዲደረግ፤

2.    በሁለቱም በኩል ለሰላሙ እንቅፋት የሚሆነውን ማንኛቸውም ነገር እንዳይደረግ ተስማምተዋል።የሰላምና አንድነት ጉባኤውም ልዑካኑን ለሰላምና አንድነቱ መሳካት ሲባል በሁለቱም በኩል ማለትም በውጭ ባሉት በኩል ሲመተ ኤጳስ-ቆጳሳት በኢትዮጵያ ባሉት በኩል ሲመተ-ፖትርያርክ  ከእርቁ በፊት እንዳይካሄድ ጠይቋል። ልዑካኑም የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ  ቃል ገብተዋል፤

3.    አደራዳሪው የሰላምና አንድነት ጉባኤም ባለአራት ነጥብ  የመፍትሔ ሐሳብ አዘጋጅቶ ያቀረበ ሲሆን የሁለቱም ወገን ልዑካን ወደላካቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ  ቀርቦ የመፍትሔ ሐሳቡን ያቀረበው የሰላምና አንድነት ጉባኤው ልዑካንን ልኮ  ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ  ጉባኤ እንዲያስረዳ ተስማምተዋል፤

4.    በሁለቱም በኩል አስቼኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተደርጎ በጥር ለሚካሄዳው 4ኛው ጉባኤ አበው ለአድነቱ መሳካት የሚረዳ የመፍትሄ ሀሳብ ይዘው እንዲቀርቡና  አባቶችን እንዲያስረዱ ተስማምተዋል።

ልዑካኑ ስለሰላም እየተነጋገሩ ሳለ አቃቤ መንበረ ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በVOA ልዑካኑ ከሚደራደሩበት  ርዕሰ ጉዳይ ጋር የተያያዘና  ለሰላሙ ሂደት እንቅፋት የሚሆን  መልዕክት ነው እንዴት ነው የሰላሙ ጉባኤ የሚቀጥለው በሁኔታው በጣም አዝነናል ሲሉ በውጭ ሀገር የሚኖሩት ልዑካን በመግለጻቸው የሰላምና አንድነት ጉባኤው አቃቤ መንበሩን አነጋግሮ መልስ ለመስጠት ቃል ገብቷል።

        የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በመላው ዓለምና በሀገራችን ኢትዮጵያ የሚኖሩ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ  ካህናትና ሕዝበ ክርስቲያን ሁሉ  ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ወደሁለቱም  አካላት ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት  ድምጻቸውን እንዲያሰሙ፣ ለቤተ ክርስቲያኑ የማያገባው ሰው የለምና ተገቢውንም ክርስቲያናዊ ዋጋ በሚያስፈልገው ሁሉ እንዲከፍሉ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን  የሰላምና አንድነት ጉባኤ ጥሪውንም ያስተላልፋል።

ከቤተ ክርስቲያንም አንድነት በፊት  በኢትዮጵያ የፓትርያርክ ሲመት፤ በሰሜን አሜሪካም ሲመተ ኤጲስቆጶሳት እንዳይካሄድ የሰላም ጉባኤው በቤተ ክርስቲያን አምላክ ስም ሁለቱን ምፍል  ይጠቃለን።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ በዳለስ እና አካባቢው ለሚገኙት አብያተክርስቲያንን ስላደረጉት አብርሃማዊ መስተንግዶ በእግዚአብሔር ስም ምስጋናውን ያቀርባል። ይልቁንም  የዳላስ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን/ ምዕመናን/ ከተጀመሮ ጀምሮ እስከመጨረሻ  ንገንዘባቸውን ጉልበታቸውንና ጊዜአቸውን የተወደደ ማሥዋእት አድርገው ስለቀረቡና ታሪክ የማይረሳው ከፍተኛ ሥራ ስለሰሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  የሰላምና አንድነት ጉባኤ ምስጋናውን  ያቀርባል።      

በመጨረሻም ለአራተኛው ጉባኤ አበው መሳካት የሰላሙን ጥረት በገንዘብ ለመርዳት የምትፈልጉ ክርስቲያኖች ሁሉ ከዚህ በሚከተለው አካውንታችን በቀጥታ ልትለግሱን ትችላላችሁ። [Ethiopian Orthodox Tewahedo Church Council for Peace - Bank Of America MD 99700101 Acct. # 4460193806663] ስለ ጉባኤው ሂደትና ታሪክ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ብሎጋችንን  ይጎብኙ።

 
http://eotc-peace-and-unity.blogspot.com/
«ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር»

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አምንድነት  ጉባኤ

 

 

 

 

 

No comments:

Post a Comment